Skip to main content
የፓርቲያችን ጥቅል ዓላማ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ ነው።

ብልጽግናስንል ፈርጀ ብዙ ትርጓሜን አዝሎ የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካ እና ማህበራዊ ገጽታ ያለው ነው። የኢኮኖሚ ብልጽግና፣ የህዝቦች መሰረታዊ ፍላጎቶች በተገቢና በዘላቂነት ለማሟላት ፈጣን እና ሁለንተናዊ ዕድገትን በማስመዝገብና ዓለም-አቀፋዊ ተወዳዳሪነት ያለው ኢኮኖሚ በመገንባት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥና የህዝቦችን ድህነትና ኋላ-ቀርነትን ለመቅረፍ መቻልን ያካተተ ነው። 

የፖለቲካ ብልጽግና ስንል ለዴሞክራሲ ባህል ማበብ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን በመገንባት፣ የህዝቦች ነፃነትና እኩልነት ተረጋግጦ፣ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውተከብረውላቸው የሚኖሩባት፣ ህብረ-ብሔራዊ አንድነቷ የተረጋገጠ፣ ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጽኑ መሰረት ላይ ማቆም ማለታችን ነው። 

የብልፅግና ራዕይ

የሚናልመዉ የኢትዮጵያ ብልፅግና ቁሳዊ፤ሰብአዊና እና የማይዳሰሱ ማኅበራዊ ሀብቶቻችንን አቀናጅተን በማነጽ የምንፈጥረዉ አቅም፤ያም አቅም በተራዉ የሚፈጥረዉ ጥሪትና የሚገነባዉ እርካታን የያዘ ሁለመናዊ ብልፅግና ነዉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መገለጫቸዉ የሆነዉን ኅብረ ብሔራዊ ማንነትና ብዝሃ እምነት ይዘዉ ፤ቱባ ባህሎቻቸዉ ተከብረዉና እንዲያብቡ ተደርገዉ፤እንደአንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ከተንቀሳቀሱ ፤አሁን ካለዉ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግር ተላቀዉ እንደበለፀጉት ሀገሮች በትዳላና በእርካታ በሰላም የማይኖሩበት ምክንያት የለም ብለን እናምናለን፡፡ 

በፖለቲካዉ የፓርትያችን ዋነኛዉ ዓላማ 

ለሁም ዜጎችዋ የምትስማማ ፤ሁሉንም ኢትዮጵያዉያን የምትመስል፤የበለፀገች ፤የብሔሮችን መብት ከግለሰብ መብቶች ጋር አጣጥማ የምታስጠብቅ ፤ጠንካራ ፌዴራላዊት ዲሞክራሲዊት ኢትዮጵያን መገንባት ነዉ፡፡ 

በኢኮኖሚዉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የኢኮኖሚ አቅሙ ፈቀደም አልፈቀደም፤ለመኖር መሠረታዊ የሆኑትን ነገሮች ማግኘት እንዳለበት ብልፅግና ያምናል፡፡ዜጎች ተመጣጣኝ ምግብ ፤መጠለያ፤ንጹሕ ዉኃ፤መሠረታዊ የጤናና ትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን አለባቸዉ ብለን እናምናለን፡፡ዜጎች እምቅ ችሎታቸዉን በመጠቀም ሀብትን በፍትሐዊነት ለመፍጠርና ለመቋደስ የሚያስችሏቸዉን የትምህርት፤የጤና እና ሌሎች አገልግሎቶች በያሉበት በጥራት ሊደርሳቸዉ ይገባል ብለን እናምናለን፡፡ 

የብልፅግና ፓርቲ መለያ እሴቶች ፦ ህብረ ብሔራዊ አንድነት፦ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት ነው፡፡ ህብረ ብሔራዊ ስንል የብሔር፣ የሐይማኖት ወይም ሌላ ማንነቶችን ያቀፈና ማንንም ያላገለለ ማህበረሰብ ማለታችን ነው፡፡ 
የዜጎች ክብር፦ ኢትዮጵያዊያንን በእኩል ዓይን የሚያይና የሚዳኝ፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብትና ነጻነት የሚረጋገጥበት፣ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊነት የሚረጋገጥበት፣ በዋና ዋና የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ሁሉም ዜጋ ውሳኔ ላይ ተሳታፊ የሚሆንበት፣ የሀብት ስልጣንና የመብት ክፍፍሉ ፍትሃዊ የሚሆንበት የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ስርዓት መፍጠር፣ አንድ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማህበረሰብ መገንባት፡፡ 
ነጻነት፦ ዜጎች የራሳቸውን ህይወት ርዕይ የመምረጥ፣ በመረጡት መንገድ የመኖር መብት እንዲረጋገጥ ማድረግ፡፡ የዜጎችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማሳደግ የሀገራችንን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት መፍታት፡፡ የዜጎችን የመሰብሰብ፣ የመደራጀት፣ የመጻፍና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመምረጥና የመመረጥ መብቶችን ማረጋገጥ፡፡